ዜና

News

ሀገር አቀፍ እጩ ሰልጣኞችን የምልመላ ሥራ እንደቀጠለ ነው

October 17, 2025  |  admin 

ጥቅምት 8 ቀን 2018 ዓ/ም
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ዋና ዳይሬክተር አቶ ባረከ ታደሰ የጥበብ ተግባራት በኢትዮጵያ ሁሉም አካባቢ ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገለጹ ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ዋና ዳይሬክተር አቶ ባረከ ታደሰ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ለብሔራዊ ጥበብ መዳረሻ›› በሚል መሪ ቃል በደቡብ ኢትዮጵያ አርባምንጭ በተካሄደው ባለው እጩ ሰልጣኞች ምልመላ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የኹሉም ኢትዮጵያውያን ቤት እንደሆነ የገለጹ ሲሆን በሙዚቃ፣ በውዝዋዜ ፣በትወና እና በሌሎች የኪነጥበብ ዘርፎች የሚገናኙበት የሚተሳሰሩበት፣ የሚወዳጁበት በዓለም ላይ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርጉበት የኪነጥበብ ቤት ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም ብሔራዊ ቴአትር ሁሉን አቀፍ እንዲኾን ለማድረግ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ተነድፎ በየክልሉ እጩ ሰልጣኞችን ለማግኘት በሁሉም ክልልና የከተማ መስተዳድር ምልመላ እያካሄደ እንደሆነ አስታውሰው ለዚሁ ታላቅ ሥራ ከ32 በላይ ብሔረሰቦች በሚገኙበት በደቡብ ክልል በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
በደቡብ ክልል ውስጥ የሚገኙት ከ32 በላይ ብሔረሰቦች የራሳቸው የኾነ ቀለም እና ድምቀት ያላቸው፣ የማይፈርሱ፣ የፀኑ፣የሚዋደዱ ፣የሚከባበሩ የኢትዮጵያ ጠንካራ ምሰሶዎች ናቸው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ከስልጠናው በኋላ ለሰልጣኞች እውቅና እንደሚሰጥ ገልጸው ተመርጠው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሚሠሩ እጩ ከያንያን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ውስጥ ደቡብ ኢትጵያን በመወከል ስለደቡብ ብሔረሰብ ያጠናሉ፣ ይመራመራሉ፤ የክልሉ ዲፕሎማት፣አምባሳደር እና የኢትዮጵያ ቀለም በመሆን ለ32 ብሔረሰቦች የመሥራት ኃላፊነትን የሚሸከም ባለአደራ ፤ ኢትዮጵያን ባህልና ትውፊት በኪነጥበብ በመግለጽ ሀገራቸውን በዓለም አደበባይ ከፍ የሚያደረጉ ይሆናሉ ሲሉ አክለዋል ፡፡
በዚህ ስልጠና ለሚመለመሉ እጩ ሰልጣኞች ልምድ ባላቸው የኪነጥብብ ባለሞያዎች የ2 ወር ስልጠና እንደሚሰጥ የገለጹት አቶ ባረከ ታደሰ የደቡብ የክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እጩ ሰልጣኞችን ለመመልመል ባዘጋጀው ምቹ ሁኔታ እና ስለተደረገው አቀባበል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትርና በወከሉት ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሥም የደቡብ ክልል ምክትል ኃላፊና የባሕል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ኦይቻ በተገኙበት ለክልሉ ምስጋና አቀርበዋል፡፡
እጩ ሰልጣኞችን በመመልመል ታላቅ ተግባር በአርባምንጭ የተገኘው ተወዳጁ አርቲስት ካሌብ ዋለልኝ በበኩሉ ለምልመላ ለታደሙ እጩ ሰልጣኞች ባስተላለፈው መልዕከት በዓለም መድረክ ላይ የሚቆሙ ዕንቁ የኢትዮጵያ ልጆችን የመፍጠር ሕልም በመያዝ በየክልሉ የሰልጣኞች ምልመላ እየተካሄደ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ የብዝኃ ህይወቷ የሚወደድ ፣የሚናፈቅ የሚከበር ነው ፡፡ለዓለም የምታሰተጋባቸው ብዙ መልዕክቶች አሏት፤ በባህላችን ውስጥ ያለ አንድነታችን፣ ውበታችን መልዕክቶችዋ ናቸው ይኽን የሚናገረው ደግሞ ኪነጥብብና ሥነጥበብ ነው ፤ዓለም በጥበብ ይመራል ሲል የገለጸው ተወዳጁ አረቲስት ካሌብ ዋለልኝ ይኽን ጥበብ በራሱ በጥበቡ ባለቤት ለዓለም ለማድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከያዘው ዓላማ አንፃር ሀገር አቀፍ ስልጠና ለመስጠት በተያዘው እቅድ መሠረት ከክልሎች አንዱ በሆነው ደቡብ ኢትዮጵያ በተመልማዮች መካከል በመገኘቱ የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡
ምልመላው እየተካሄደ ያለው በየክልሉ እና በየከተማ መስተዳድሮች ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት እጩ ተመልማይ አቅራቢነት መሆኑ ይታወቃል፡፡
Scroll to Top