ዜና

News

ታላቁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የተመሠረተበት 70ኛ ዓመት በታላቅ ድምቀት ተከበረ

November 12, 2025  |  admin 

ኅዳር 3 ቀን 2018 ዓ/ም
አዲስ አበባ
ታላቁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የተመሠረተበት 70ኛ ዓመት በድምቀት ተከበረ
በ1948 ዓ/ም ቀዳማዊ ኃይላስሴ ቴአትር ቤት በሚል ስያሜ የተመሠረተው ታላቁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር 70ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ ኅዳር 3 ቀን 2018 አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሞያዎች ጥሪ የተደረገላቸው ታዳሚያን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡ ዕለቱን በማስመልከት የማርሽ ባንድ የመክፈቻ ዝግጅቱን በማስጀመር ያጀበ ሲሆን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነጥበብና ሥነጥበብ ፈጠራ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ረ/ፕ ነብዩ ባዬ በዘግጅቱ መክፈቻ ንግግራቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከተመሠረተበት ጊዜ ጅምሮ የቴአትር ቤቱን ህልውና አስጠብቀው በኪነጥበብ ልህቀት የህዝብን ባህልና ታሪክ ቀርሰው ላሻገሩት የኪነጥበብ ሰዎች፤እንዲሁም ቴአትር ቤቱን ለመሠረቱልን ለቀዳማዊ ኃይለስላሴ ምስጋና ይገባቸዋ ብለዋል፡፡
በዘመናት ውስጥ ይኽን የኪነጥበብ ወረት ታላላቆቻችን እንዳሻገሩልን ሁሉ እኛም መጠበቅና ማስቀጠል አለብን ያሉት ክቡር ረ/ፕ ነብዩ ባዬ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር እንደስሙ የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሆኑ አንደአለፉት ዘመናት ሁሉ በሁሉም አቅጣጫ ችሎታና ክህሎት ያላቸው ከያኒያን መዕከል በመሆን የአንጋፋ የኪነጥበብ ሰዎች ማፍሪያና መፍለቂ ተቋም ሆኖ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ዋና ዳይሬክተር እጩ ዶ/ር ክቡር አቶ ባረከ ታደሰ በበኩላቸው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አመሠራረትን የኋላ ታሪክን አስታውሰው በ70 ዓመታት የኪነጥበብ ጉዞ ውስጥ ደማቅ አሻራቸውን ያሳረፉትንና ለዛሬ ያሻገሩትን የኪነጥበብ ሰዎች አመስግነዋል፡፡
በዕለቱ ቴአትር ቤቱ ከተመሠረተ ጀምሮ የታዩ ቴአትሮችና ሙዚቃዎች ቅንጭብ ዶክመንተሪ፣ የፎቶ እና የአልባሳት ኤግዚቢሽን እንዲሁም የቫራይቲ ኦኬስትራና ፤የባህል ቡድን ስራዎች በአርቲስት ተስፋዬ ገብረሃና የተዘጋጀ የአንጋፋው አርቲስት ጌትነት እንየው ‹‹ወይ አዲስ አበባ ›› ቅንጭብ ቴአትር ያቀረበ ሲሆን የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርጸ ፍሬ ስብሃት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከተመሠረተ ጀምሮ በኪነጥበብ ጉዞ በየሥርዓቱ የሄደበትን ዳሰሳዊ ጥናት አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር 70ኛ ዓመት ክብረ በዓል በተለያዩ ደማቅ ዝግጅቶች ቀጣይነት ያለው ሲሆን 70ኛ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ ከሕዳር 13 ቀን 2018 ጀምሮ የተለያዩ ቴአትሮች በነፃ ለታዳሚያን ይቀርባሉ፡፡
Scroll to Top