ዜና

News

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር 70 ዓመታት የኪነ-ጥበብ ጉዞ በ7 ቀን” ዝግጅት ተጠናቀቀ

November 29, 2025  |  admin 

ኅዳር 20 ቀን 2018 ዓ/ም
አዲስ አበባ
የታላቁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር 70ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን አስመልክቶ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር 70 ዓመታት የኪነጥበብ ጉዞ በ7 ቀን” በሚል መርሃ ግብር ሲቀርብ የነበረው ዝግጅት ዛሬ ተጠናቀቀ፡፡
ኅዳር 3 ቀን 2018ዓ/ም የምሥረታ ቀኑን በዕለቱ በተለያዩ ዝግጅቶች በማክበር ከኀዳር 13 ቀን /2018 ዓ/ም እስከ ኅዳር 20/2018 ዓ/ም ለመላው የኪነጥበብ ወዳጆች ቴአትር ፣የፎቶና የአልባሳት ዓውደ ርዕይ በነፃ ሲቀርብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ዛሬ ኅዳር 20 ቀን 2018 ዓ/ም ከረፋዱ 4፡00 ጀምሮ በረዳት ፕሮፌሰር አክሊሉ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሙዚቃ ሥራ ከየት ወዴት”፤በዶ/ር ግሩም አረዳ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር እና ዲጂታል ዘመን አዳዲስ የመድረክ ዕድሎችና ፈተናዎች”፤
በዕጩ ዶክተር ማንያዘዋል ጌታቸው “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አስተዳደር ከ1948 -2015 ዓ/ም” በሚል ርዕስ ጥናት የቀረበ ሲሆን ከታዳሚያን ለቀረቡ ጥያቄና አስተያየቶች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
በአውደ ጥናቱ ጅማሬ የእንኳን ደህና መጣችሁ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቴአትር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዕጩ ዶ/ር ባረከ ታደሰ የቴአትር ቤቱን የኋላ ታሪክ አስታውሰዋል፡፡ ቴአትር ቤቱ ታላቁን የጥበብ ሰው ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህንን ጨምሮ ታላላቅ የኪነጥበብ ሰዎች የወጡበት የልህቀት ማዕከል፤ የጥበባውያን ቤተመንግሥት ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ታሪኩን ማጥናት ፤ምን እንደነበረ፤ምን እንደተቋረጠ፣ ምን መቀጠል እንዳለበት አመላካች በመሆኑ ማጥናትና መተንተን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ከሰዓት በኋላ በቀጠለው ማጠናቀቂያ ዝግጅት የማርች ባንድ ዝግጅቱን ያጀበ ሲሆን አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሞያዎች፣በርካታ ታዳሚያን በተገኙበት በመራሒ ተውኔት አስታጥቃቸው ይሁን የተፃፈው “Love and Peace” የተሰኘ ቴአትር ፤ የቫራይቲ ኦኬስትራ የተለያዩ ጥዑመ -ዜማዎች፣ ቅንጭብ ቴአትር፣ ጭረት የተሰኘ ዳንስ የቀረበ ሲሆን የእውቅና የመዘጊያ ሥነ-ስርአት ተካሂዶ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር 70 ዓመታት የኪነጥበብ ጉዞ በ7 ቀን” በሚል መርሃ ግብር ሲቀርብ የነበረው ዝግጅት በደማቅ ሥነ ስርዓት ተጠናቅቋል፡፡
Scroll to Top