ዜና
News
‹‹ዴጊያ›› ትውፊታዊ ቴአትር፡- ይኽ የተከበረ ታላቅ ህዝብ!
October 22, 2025 | admin
ጥቅምት 13 ቀን 2018 ዓ/ም
በማይረሳ ትውስታ ጉዞ ወደ መኤኒት ማህበረሰብ የተደረገው ጥር 22 ቀን 2017 ዓም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ልዑክ የዴጊያ ትውፊታዊ ቴአትር ግብአትን ከምንጩ ለማሰብሰብ ወደ ደቡብ ምዕራብ ሲያቀና ህዝቡ ጎዳናዎቹን ፣አደባባዮቹን የኢዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር እንኳን ደህና መጣችሁልን ብለው መንገዶቻቸውን አስውበው፣በፎቶ እንደሚታየው ማህበረሰቡ ግልብጥ ብሎ ነበር በየደረስንበት በቆይታችን የተቀበለን፡፡ ይኽ ታላቅና የፍቅር ሰንዱቅ ህዝብ የሚያስደንቅና ልንጋራው የተገባ የድንቅ ባህል፣እሴት፣ትውፊት ባለቤት ነው፡፡
ውድ የኪነጥበብ ወዳጆች በዚህ ደግ፣ የፍቅርና የአብሮነት ምሳሌ በሆነ ታላቅ ህዝብ ትውፊት ላይ ተመስርቶ የተጻፈው እጅግ ተወዳጅ ‹‹ዴጊያ ›› የተሰኘ ትውፊታዊ ቴአትር ዘወትር ቅዳሜ በ8፡30 ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር እንደሚቀርብ ስንገልጽ በታላቅ ደስታ ነው፡፡
ጥቆት በለደቡብ ምዕራብ ኦሞ ዞን ስለሚገኘው
ስለመኤኒት ማህበረሰብ በጥቂቱ
ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ካሉት 13 ነባር ብሔረሰቦች አንዱ የመኤኒት ብሔረሰብ ነው።የመኤኒት መደበኛ ቋንቋው ያደረገው የመኤኒት ብሔረሰብ ከኦሞ (ፏጫ) በስተ ምዕራብ በኩል ከዲዚ፣ ሱሪና ዝልማሞ (ባሌ) ብሔረሰቦች በተጨማሪ ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር ሆነው በምዕራብ ኦሞ ዞን ውስጥ የመኤኒት ጎልዲያ፣ የመኤኒት ሻሻ፣ ጋቺት፣ ጎሪጌሻ እና ማጂ ወረዳዎች እና በጉራፈርዳ ወረዳ በሰፋት እንድሁም በካፋ ዞን ጎባና ዴቻ ወረዳዎች በጥቂት ቀበሌያት ይኖራሉ።
ጥናቶችና ነባራዊ እውነታዎች እንደሚያመለክቱት የመኤኒት ማህበረሰብ ከክልሉ ውጪ በደቡብ ኢትዮጵያ ደቡብ ኦሞ ዞን ሰላማጎ ወረዳ በስፋትና ሌሎች አካባቢዎችም እንደሚኖሩ መረጃዎች ያሳያሉ።
በስራ ወይም በየትኛውም ምክንያት ሰብሰብ ባሉ ሰዎች መካከል ድንገት ከተገኘ ”አሻም ዞጊያ…. ቲሻና…” በሚል ደጉ ሰላምታቸው የሚታወቁት የመኤኒት ማህበረሰብ የሚኖሩባቸው ወረዳዎች ስነ ምህዳራዊና ተፈጥሮአዊ ሁኔታቸው ሲታይ ከካፒ ተራራ እስከ ያርጣ ሸለቆ ተፈጥሮ ካደላት ከትልቁ ሾሩም ወንዝ፥ በተመቸ አየሩ ለኑሮ ከሚመረጥ፥ በጤፍ ከሚታወቅ የጨበራው መሬት፥ የደጋግ ህዝቦች መኖሪያ ምድረ ጎልዲያ -ባቹማ፤ከኤሌ ኬኒ ተራራ ዉበት እስከ ዳል ፏፏቴ፥ ለብዙዎች ማረፊያ ሆኖ ‹‹ማረፊያ›› የሚል መጠሪያ ያገኘ፥ ነው፡፡ኮረሪማ፣ማር፣ማሾ ማእድኑ ወዘተ…ገና እንደተከደነ ያለ ተከፍቶ ኢኮኖሚን ለማደርጀት መንግሥትን የሚጠብቅ አንጡራና ያልተነካ ድንግል ሀብት ነው ፡፡
ከናንጣራ ዳገት ጥንካሬን አስተማሪ፥ ከጉሚ ተራራ አናት ሻሽ የሚመስል ደን ሻሻ የተባለለትን የኦሞ ወንዝ ተጋሪ፥ በካቲላው ምግብ እንግዳን ተቀባይ፥ ማብቀል ከማይሰለቸዉ ለም መሬት ምድረ ሻሻ -ጀሙ።
በልዩ ጣዕሟ ዓለምን የማርከው የጌሻው ቡና መገኛ፥ የመሪነት ጥበብ ለትውልድ አሻጋሪ፤ የመኤኒት ነገስታት ሻያና ቢሌሙ፤ ድንበር አስጠባቂ የቀኝ አዝማቹ ጋሊ ሀገር ነው፡፡
የመኤኒት ማህበረሰብ የራሳቸው የሆነ የተከበረ ባህል፤ ታርክ፤ ቅርጽ፤ ቋንቋ … ወዘተ እሴቶች አሉት። እነዚህ እሴቶች የሚያስተዋውቁበት የራሳቸው የሆነ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ ጭፈራ፣ ለቅሶ እና አስደማሚ ባህላዊ የዳኝነት ስነ-ስርዓት አላቸው።
በመኤኒት አካባቢ የተለያዩ ባህላዊ ቅርጾች፣ ተፈጥሯዊ ሃብቶች፣ ለሁሉም ዓይነት የግብርና ስራ የተመቸ ለም መሬት እና አመቱን ሙሉ የሚፈሱ ትላልቅ ወንዞች በዋናነት ኦሞ(ፏጫ)፣ ሾሩም፣ ኪሉ፤ ዳል፤ ብላንግና ካሹ ወንዞች ይገኙበታል።
መኤኒት የእንግዳ ተቀባይነትና አክባሪነት ባህሉ ምስክርነት የማያሻው በቀደምት አባቶቹና የአሁኑ ትውልዱ ልብ የታተመ የማይገረሰስ ሕግ ነው።
ከዞኑ ነባር ብሔረሰቦች በተጨማሪ መኤኒቶች ከመላው ኢትዮጵያውያን በዋናነት የቤንች፣ የሸኮ፣ የአማራ፤ የካፋ፣ የኦሮሞ፣ የሲዳማ፣ የከንባታ፣ የወላይታ፣ … ወዘተ ብሄረሰቦች ጋር ከገጠር እስከ ከተማ አብረው ተደጋግፈው ይኖራሉ፣ ይጋባሉ፣ በጋራ ይሠራሉ።
መኤኒቶች ሰው ሰው ከመሆኑ ባለፈ ሌሎች ብዝሃ ማንነቶቹ በተፈጥሮና የዕድገቱ አካባቢ የተቸሩ በረከቶች በመሆኑ ልዩ አክብሮት ያስፈልጋል በሚለው እምነቱ የማንነቱ መጠሪያ ትርጉሙንም ”ሰው/መኤኒት/” የሚል ትርጉም አለው።
በሌሎች ማህበራዊ መስተጋብር በእርሻ ስራ፣ በእንስሳት እርባታ፣ በማዕድን ቁፋሮ፣ በንብ ማነብና በንግድ ሥራዎች …ወዘተ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከየትኛውም የሰው ዘር ጋር ተቆራኝቶ በአብሮነት፣ በመቻቻልና በመግባባት የሚኖር ፍቅር ብቻ የሆነ ማህበረሰብ ነው።
ከትልቅ እስከ ትንሽ አንደበት የማይጠፋው፥ ቢያውቅህም ባያውቅህም የሚቸርልህ ዉስጣዊ የልብ ቃላቸው “አሻም ዞጊያ/መንዲያ/ውንጂያ…ትሻና ናይ!” የሚለው ደጉ ሰላምታቸው ነው።
ከሌላ አከባቢ እንደመጣህ በቀላሉ ይለዩና ከእነሱ ወገን ካልሆንክ ሌላ ጣጣ ውስጥ ሳይገቡ በአንድ ላይ አማራ ብለው ይደመድሙና “አሞሮዲያ”በሚል የፍቅር መጠሪያ ከልብ በፍቅር ይጠሩሃል። ያቅፉሃል፡፡
ደም ከማፍሰስ እስከ ህይወት መጥፋት የደረሱ ግጭቶች ”አሻ” በሚል ባህላዊ የዕርቅ ሥነስርዓት፣ በግለሰቦችና ማህበረሰቦች መካከል ጥልን እስከወዲያኛው በዚህ የእርቅ ሥንስርዓት ይሸኛሉ። ”ባል” የሚል ስያሜ ባለው የዳኝነት ዛፍ ስር የትኛውም ልዩነቶችና ስሞታዎች በአከባቢው የሀገር ሽማግሌዎችና ባላባቶች ዳኝነት ይሰጣሉ።
የ ‹‹ዴጊያ›› ትውፊታዊ ቴአትር በአንዱዓለም አባተ ተጽፎ መሠረታዊ ግኝትም ይኽ ባሕላዎ የእርቅ ሥነስርዓት ነው፡፡
በዶ/ር አንዱአለም (ያጸደ ልጅ ) ተጽፎ በኢስጢፋኖስ ከበደ እና በቴዎድሮስ ይደግ የተዘጋጀው፣ ራሄል ተሾመ መሐመድ ረዳት አዘጋጅ የሆነችበት ‹‹ዴጊያ›› ትውፊታዊ ቴአትር የዚህ የተከበረ እንግዳ ተቀባይና የሰው ዘርን አክባሪ የሆነ ማህበረሰብ ትውፊት ላይ ተመስርቶ የተጻፈ ትውፊታዊ ቴአትር ነው፡፡ ሁላችሁም ሳታመነቱ፣ቀጠሮ ይዛችሁ ተመልከቱት፡ ታተርፉበታላችሁ፡፡
* **//***
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽነ ሥራ አስፈፃሚ