ዜና
News
የአንጋፋዋ አርቲስት አሰለፈች በቀለ ነቅዐጥበብ አጭር የሕይወት ታሪክ
March 26, 2026 | admin
አርቲስት አሰለፈች በቀለ ነቀዐጥበብ ሴቶች በአደባባይና በመድረክ መታየት እንደ ነውር በሚታይበት በዛ ዘመን የዘመኑን ተግዳሮት ጥሰው ከወጡትና ዛሬ ላይ ለበርካታ ሴት አርቲስቶች አርአያ ከሆኑት ቀደምትና አንጋፋ የጥበብ ሰዎች ውስጥ አንዷ እና ለኪነጥበቡ ዘርፍ ማበብ አሻራዋን ያሳረፈች ታላቅ አርቲስት ናት፡፡
አንጋፋዋ አርቲስት አሰለፈች በቀለ ከአባቷ ከአቶ በቀለ ነቀዐ-ጥበብ እና ከእናቷ ከወ/ሮ በላይነሽ አድማሱ በ1940 ዓ/ም በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ ደጃች ውቤ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወለደች፡፡
ከልጀነቷ ጀምሮ ለጥበብ ከፍተኛ ፍቅር የነበራት አርቲስት አሰለፈች በቀለ ባላት ተሰጥኦ እና የላቀ ፍላጎት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከታህሳስ 8 ቀን 1958 ዓ/ም ጀምሮ በሁለገብ የባሕል ተጫዋችነት ተቀጥራ በጡረታ እረፍት አስከተገለለችበት እስከ ታህሳስ 1ቀን 1995 ዓ/ም ድረስ ለ 37 ዓመታት በቴአትር ቤቱ በከፍተኛ የሥራ ፍቅር ፣ትጋትና እና የሞያ ዲስፕሊን አገልግላለች፡፡
ቴአትር ቤቱ ያካሂድ በነበረው የማያቋርጥ የፈጠራ ሥራ ውስጥ ችሎታዋን ሳትቆጥብ በድምጻዊነት፣በተወዛዋዥነት ፣በተዋናይነት ፣በውዝዋዜ አሰልጣኝነትና አዘጋጅነት በማገልገል፤ የሥራ ድርሻዋን በከፍተኛ ኃላፊነትና ትጋት የተወጣች፣ በሥራዋ አርአያነት ያላት በመሆንዋ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ላበረከተችው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጉን የጥበብ ሰውነቷን፤ሥራ ወዳድና ትጉህ መሆንዋን የሚገልጹ በርካታ የምሥክር ወረቀቶችና ደብደቤዎች ተበርክተውላታል፡፡
አርቲስት አሰለፈች በቀለ የሀገረሰብ ሙዚቃዎችን በ14ቱም ጠቅላይ ግዛት በመዘዋወር የብሔር ብሔረሰቦች ዕምቅ ጥበብ በማሳወቅ፣በማዝናናት፣ሀገር የጦርነት ፈተና በገጠማት ጊዜ ግንባር ድረስ በመሄድ ሠራዊቱን በማነቃቃት እና በመደገፍ ለሀገርዋ ከፍተኛ ሥራ ሠርታለች፡፡ድንበርና ከለል ሳይገድባት፣አድማስ ሰንጥቃ በሴኔጋል፣ በሌጎስ፣በናይጄሪያ፣ በአልጄሪያ፣በደቡብ አፍሪካ ፣በሱዳን፣ በየመን፣ በፈረንሳይ፣በሜክሲኮ፣ በጀርመን፣ በካናዳ፣ በኩባ፣በሆላንድ፣እና በሌሎች የውጭ ሀገራት ከባሕል ቡድኑ ጋር በመጓዝ የኢትዮጵያን ባሕል አስተዋውቃለች፣ የሀገርዋን ገፅታ ከፍ አድርጋ አውለብልባለች፡፡
አርቲስት አሰለፈች በቀለ በባሕል ድምጻዊነት፣ከተወዛዋዥነት የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን ሥራዎች ከመጫወቷ ባሻገር በተዋናይትነት፡-“ውድቅት”፣ “ሀምሌት”፣ “ስስታሙ መንጠቆ”፣”የከተማ ባላገር”፣”ያስቀመጡት ወንደላጤ” በተሰኙ እና በሌሎች ቴአትሮች ላይ የተወነች ሁለገብ እና ኮከብ የዘርፉ ባለሞያ ነበረች፡፡
ሞያዋን ለተተኪው ትውልድ ለማስተማር፤ልምዷን ሳትሰስት ለወጣቶች ለማካፈል በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት አንጋፋ የኪነጥበብ ሰዎች መካከል አንዷ የነበረችው አርቲስት አሰለፈች በቀለ ለተጎዳ፣ለተገፉ፣ለተበደለ ሁሉ ፊት ለፊት ስለእውነት የምትሟገት ቀና እና ትሁት ልብ ያላት አርቲስት እንደሆነች የሞያ አጋሮችዋ ይገልጻሉ፡፡
አሰለፈች ለትምሕርት ካላት ታላቅ ፍቅር የተነሳ እየሠራች በመማርም ጭምር የአንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ተከታትላለች፡፡
አርቲስት አሰለፈች በቀለ ነቀዐጥበብ የሁለት ሴት ልጆች እናት፣የሦስት የልጅ ልጆች አያት ስትሆን ይህች ታላቅ እና ሁለገብ የባሕል ሙዚቃ ኮከብ ተጫዋች ባደረባት ሕመም በህክምና ስተረዳ ቆይታ በሀገረ አሜሪካ መጋቢት 10 ቀን 2018 ዓ/ም በተወለደች በ78 ዓመቷ በሥራዎችዋ ሕያው ሆና ከዚህ ዓለም ድካም በክብር አርፋለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ለ ቤተሰቦችዋ፣ለሥራ ባልደረቦችዋ፤ለወዳጅ ዘመዶችዋ ለአድናቂዎችዋ ለመላው ሕዝብ መጽናናትን ይመኛል፡፡