ዜና
News
ዓለም ዓቀፍ ክብረ በዓላት በጋራ ተከበሩ
December 10, 2025 | admin
ታህሳስ 1/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር እና የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ተቋም አመራሮችና ሠራተኞች በጋራ ዓለም አቀፍ የሕጻናትና የጸረ- ጾታዊ ጥቃት እና የኤች አይ ቪ/ኤድስ/ ቀንን ራ አከበሩ ፡፡
“የህፃናት ጥበቃና የመጫወት መብት ለሁሉም ህፃናት”“ፆታዊ ጥቃትን የማይታገስ ማሕበረሰብ ለትውልድ ግንባታ”፣”ተግዳሮቶችን በመቋቋም የኤች አይ ቪ ኤድስ ምላሽን በዘላቂነት እናረጋግጥ” በሚሉ መሪ ቃሎች ሦሰት ዓለም ዓቀፍ በዓላት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የተከበረ ሲሆን በመግቢያ ዝግጅቱ ላይ የቴአትር ቤቱ የረቂቅ ሙዚቃ ቡድን ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
የአንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬ ስብሐት ሕጻናት በመልካም ሥነ-ምገባር ታንጸው እንዲያድጉ ከለጋ እንደሜያቸው ጀምሮ አዕመሯቸው ላይ መሥራት እንደሚያስፈለግ፤በሞራል በሥነ ምግባር አንጾ ለማሳደግ የሕጻናት መጽሐፍት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለቸው ባለፉት ዘመናት ትውልድን የቀረጹ የክቡር ከበደ ሚካኤል ተረትና ምሳሌ መጽሐፍን ዋቢ አድረገው ገልጸዋል፡፡
አዕምሮው ላይ የተሠራ ትውልድ ከሴቶች ጥቃት የታቀበ ፣በሕጻናት ጥበቃ ላይ ንቁ እና ሰላማዊ ማሕበረሰብ ለመፍጠር መሠረት እንደሆነ በንግግራቸው ያመላከቱት ዋና ዳይሬክተሩ እንዲህ ዓይነት ዓለም አቀፍ ሁነቶች ሲከበሩ አስተማሪ ክዋኔዎች እና መልዕክት አዘል ግንዛቤ በሚያስጨብጡ ተግባራቶች ተካተው፤ ትኩረት ተሰጥቶ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ የዛሬው ጅማሮ የሚያሳይ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በዕለቱ በሕጻናት አስተዳደግ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የመወያያ ጥናታዊ ጽሑፍ በረ/ፕ ታምራት ዘላለም የቀረበ ሲሆን ለውይይት የቀረበው ጥናት ከፍተኛ ግንዛቤና መነቃቃት የፈጠረላቸው መሆኑን ተሳታፊዎች በውይይቱ ገልፀዋል። በተያያዥ እንዲህ አይነት ሕይወት መር ስልጠና ተከታታይነት ባለው ሁኔታ ቦታና ጊዜ ተመቻችቶ ለተቋማት ብቻ ሳይሆን ለማሕበረሰቡ ተደራሽ ሊሆን ይገባል ሲሉ በአስተያየታቸው ገልጸዋል፡፡
በዕለቱ ‹‹ሴቶች ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት ላለመፈጸም እና ጥቃት በሴቶች ላይ ሲፈጸምም ዝም አልልም››በሚል ዓለማቀፋዊ ቃል ኪዳን መሠረት ወንዶች ነጭ ሪቫን፤ ሴቶች ቀይ ሪቫን አስረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚዎች ወ/ሮ ሀገሬ መኮንን እና ወ/ሮ ሠላማዊት ዞይት ሴቶችና ህጻናትን በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት የዕለቱ ክበር በዓል ዝገጅት ተጠናቋል፡፡