ዜና

News

ብሔራዊ ቴአትር ጉብኝት – ወርቀሰሙ ማሞ ለውጥን እና ተነሳሽነትን ገልጸዋል

December 31, 2025  |  admin 

አመራሩ ለውጥ ላይ ነው፡የሥራ ተነሳሽነት አለ፡ጅምሮቹ ይኽን ያሳየሉ፡፡የተከበሩ ወርቀሰሙ ማሞ
ታህሳስ 21 ቀን 2018 ዓ/ም
በክብርት ወ/ሮ ወርቀሰሙ ማሞ የጤና ማህበራዊ ጉዳዮች ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተመራ ልዑክ ታህሳስ 21 ቀን 2018 ዓ/ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በመገኘት ጉብኝትና ምልከታ አደረገ፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር 70ኛ ዓመቱን ተንተርሶ በቴአትር ቤቱ የተቋቋመውን የፎቶና የአልባሳት ሙዚየም ጉብኝት አደርጓል ፤እንዲሁም በአዲሱ ቴአትር ቤት ላይ ምልከታ ያደረገ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የ8 ዓመት የስኬት ጉዞ እና ወደፊት ትኩረት የሚሹ ስትራቴጂክ ጉዳዮች›› በሚል ርዕስ በቴአትር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር በዕጩ ዶ/ር ባረከ ታደሰ የተዘጋጀ ዳሰሳዊ ምልከታ ለልዑኩ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
አመራሩ በለውጥ ላይ ነው፡፡የሥራ ተነሳሽነት አለ፡፡ጅምሮቹ ይኽን ያሳየሉ ያሉት የተከበሩ ወርቀሰሙ ማሞ ፤ይህ ዘርፍ በዜማ፣ በጽሁፍ ፣በቴአትር፣ ሰላምን፣ አብሮነትን የሚገነባ የኢትዮጵያን ገፅታ የሚቀይር ማርሽ ቀያሪ ዘርፍ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ዘርፉ የሚሰራው አዕምሮ ላይ እንደመሆኑ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያሳይ፤ አብሮነትንና ወንድማማችነትን የሚያመጣ በመሆኑ በዘርፉ ልንጠቀምበት ይገባል ያሉት ክብርት ወርቀሰሙ ማሞ በጉብኝቱ የተመለከቱት ሙዚየም ደስ የሚያሰኝና መደራጀቱ ትልቅ የሥራ ተነሳሽነትና ሀሳብ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን ቴአትር ቤቱ ያሉት መረጃዎች፤የጽሁፍ ዶክመንቶች በዘመናዊ መንገድ ዲጂታላይዝድ መደረግ እንዳለበት በውይይቱ አመላክተዋል፡፡ አያይዘውም የአዲሱ ቴአትር ቤት ግንባታ ክትትልን በተመለከተ ከሚኒስትሮች ጋር በመነጋገር ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
የጤና ማህበራዊ ጉዳዮች ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ም/ ሰብሳቢ ዶ/ር ታደለ ቡርቃ በበኩላቸው የቴአትር ቤቱ ትልቁ ጉዳይ እና ሀብት ተመልካች ነው፤ በተመልካች ልማት ላይ ጠንክሮ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ አያይዘውም የሥራ ተነሳሽነት ፣ኢትዮጵያን የመሰለ ቤት እና ባለሞያ፣ እንዲሁም ቅንጅታዊ ሥራ በተግባር የተገለጠ እንዲሆን መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ማብራሪያ የሚፈልጉበትን ጉዳዮች በማንሳት ማብራሪያ የተሰጠበት ሲሆን ባሉት ጅምር ሥራዎች የተሰማቸውን ደስታ ሳይሸሽጉ ጅምሮችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸው ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ከጎናችሁ ነን ብለዋል። —-//——-
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አሥፈጻሚ
Scroll to Top